
የመጀመሪያ ሳምንት፣ 3ኛ ቀን
የመጀመሪያ ሳምንት 3ኛ ቀን ቀጣይነት ያለው የCEO የጥበብ ምክር ዕለታዊ እና የልብ ለልብ ግንኙነት የግል ድጋፍ አገልግሎት ለለውጥ ሥልጠና ቀጥሏል!
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2018 ዓ.ም
የኢትዮ ጥሪት ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳሻው ተገኘ ቀደም ሲል ከፈጻሚዎች ጋር ባደረጉት ውይይት መሠረት ለሁሉም አመራሮችና ፈጻሚዎች “የCEO የጥበብ ምክር ዕለታዊ እና የልብ ለልብ ግንኙነት የግል ድጋፍ አገልግሎት ለለውጥ ስልጠና” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት ሥልጠና ለሦስተኛ ቀን ቀጥሏል።
የሥልጠናው መርሃ-ግብር በመጀመሪያው ሳምንት ‘ማንነት’፣ በሁለተኛው ሳምንት ‘የባለቤትነት ስሜት አስተሳሰብ’፣ በሦስተኛው ሳምንት ‘ተጠያቂነት’ እና በአራተኛው ሳምንት ደግሞ ‘ኃላፊነት’ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ የመጀመሪያው ሳምንት 3ኛው ቀን ሥልጠና “ማንነት” በሚለው ርዕስ ሥር ከማኅበሩ አርማ (ሎጎ) ጋር በተያያዘ ለዘላቂ ለውጥ የሚረዳ ልዩ ሥልጠና ተሰጥቷል።
“ሥልጠና ሰውን ይገነባል፣ ሰው ተቋምን ይገነባል፣ ተቋማቶች ደግሞ ሀገርን ይገነባሉ” ያሉት አቶ እንዳሻው ተገኘ፣ የአንድን ተቋም ማንነት በመግለጽ ረገድ የተቋሙ አርማ (ሎጎ) ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
የራዕይ ትርጉም ግለሰብን፣ ማኅበረሰብንና አገርን በማበልጸግ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የገለጹት አቶ እንዳሻው የማኅበሩ ራዕይም “ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች የመነሻና የንግድ ሥራ ማስፋፊያ ካፒታል አቅርቦ ሕልማቸውንና ተስፋቸውን እውን በማድረግ የበለጸገ ማኅበረሰብን ማየት” መሆኑን በድጋሚ አብራርተዋል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራት በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገትና የገበያ ዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገለጹት አቶ እንዳሻው በወጣቶች ላይ ትኩረት ማድረጋችንም ለዚሁ ነው ብለዋል። ወጣቶች የአንድ አገር አምራች ኃይል ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የማኅበሩ ራዕይ ለወጣቶች ትልቅ ትኩረት በመስጠትና አቅማቸውን በመገንባት የራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው ብለዋል።
የማኅበሩ አርማ (ሎጎ) ቀለማት አረንጓዴ፣ ቢጫና ነጭ መሆናቸውን በመጥቀስ እንዲሁም የእያንዳንዱን ቀለም ትርጉም ከማኅበሩ ማንነት ጋር በማገናኘት አቶ እንዳሻው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከአርማው ማብራሪያ ጎን ለጎን የእያንዳንዱን አባል ችግር በመፍታት ለአገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት መስራት አለብን ሲሉም አሳስበዋል።
ሁላችንም 100% የባለቤትነት ስሜትን፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በመላበስ የአባላትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አለብን ያሉት አቶ እንዳሻው ሰራተኞችም ሥልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የማኅበሩ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙላቱ በዕደ በበኩላቸው ሁልጊዜም በባለቤትነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት አባላትን ማገልገል እንደሚገባ ገልጸው በሥልጠናው መደሰታቸውንና ሁሉም ሰው ሥልጠናውን ወደ ተግባር ሊቀይረው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመጨረሻም አቶ እንዳሻው ሁሉንም አመራሮችና ፈጻሚዎች አመስግነው የመጀመሪያ ሳምንት 3ኛ ቀን ሥልጠና ተጠናቋል።
ለተጨማሪ መረጃ:
Ticktok: tiktok.com/@terit.saccos
You tube: www.youtube.com/@teritmedia
Telegram: t.me/ethioterit21
Facebook: www.facebook.com/profile.php?id=100070815460611
Website: www.ethioterit.com
Email: info@ethioterit.com
Short Code: 9124



